የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት የንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ የኢትዮጵያ አክሬዲቴሸን አገልግሎት ያለበት የቢሮ ጥበት ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል አለ፡፡ ለቋሚ ኮሚቴው አባላት በአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ስለ አገልግሎቱ የሥራ እንቅስቃሴ ገለጻ ተደረገለት፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት የንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ሰብሳቢ ወ/ሮ አይሻ ያህያ የተመራው የቋሚ ኮሚቴ አባላት ጥር 23 ቀን 2014ዓ.ም በኢትዮጵያ አክሬዲቴሸን አገልግሎት የመስክ የሥራ ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን ስለ አገልግሎቱ የስራ እንቅስቃሴ በአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ አርአያ ፍስሃ ገለጻ ተደርጎላቸዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ ለቋሚ ኮሚቴው ባደረጉት ገለጻ የኢትዮጵያ አክሬዲቴሸን አገልግሎት ስራዎቹን በዋናነት በስድስት ቋሚ ምሰሶዎች የተመሰረተ መሆኑንና ይህም ቀጣናዊና ዓለም አቀፍ ትስስር፣ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው የአክሬዲቴሸን አገልግሎት፣የሰነድ ዝግጅትና ትግበራ፣ቀጣይነት ያለው መሻሻል፣የአክሬዲቴሸን ገበያን መፍጠርና ብቃትና መሻሻልን መሰረት ያደረገ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
ይህንን መሰረት አድርጎ የኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን አገልግሎት ባለፉት አስር ዓመታት በሶስት መስኮች ማለትም በሕክምና ላቦራቶሪ ISO 15189፣ በፍተሻ ላቦራቶሪና ISO/IEC 17025 በኢንስፔክሽን ISO/IEC 17020 ዘርፎች ተቃሙ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተገምግሞ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ማግኘቱን የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ በስርዓት ሰርቲፍኬሽንም ISO/IEC 17021 በዘንድሮው ዓመት ግምገማ ማድረጉንና በቀጣዮቹ አራት ወራት ዓለም አቀፍ እውቅና እንደሚያገኝ አብራርተዋል፡፡
በሰነድ ዝግጅት ረገድ ከ250 በላይ የተለያዩ ሰነዶችና ፎሞች መዘጋጀታቸውን፣በሰው ኃይል ስልጠናና ዝግጅት ረገድ 101 የትርፍ ሰዓት አሰሰሮች በተለያዩ ዘርፎች ማሰልጠን መቻልንም ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ አክሬዲቴሸን አገልግሎት የአክሬዲቴሸን አገልግሎት ለመስጠት በቂ ዝግጅት ቢኖረውም የአክሬዲቴሸን ፈላጊው ቁጥር ግን የተፈለገውን ያህል እንዳልሆነና ይህም ከተሳሳተ ግንዛቤ በመነሳት የመጣ እንደሆነ ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡
አክሬዲቴሸን አስገዳጅ አይደለም የሚለው አመለካከት የተሳሳተ ትርጓሜ እንደሰጠው የተናገሩት ዋና ዳይረክተሩ ተቆጣጣሪው አካል ተቋማት ወደ አክሬዲቴሸን እንዲመጡ የማስገደድ ስልጣን እንዳለው የአክሬዲቴሸን ተቋሙ ግን ራሱ ከሳሽ ራሱ ዳኛ አይሆንም ብለዋል፡፡
በዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ የተደረገላቸው የቋሚ ኮሚቴው አባላት የአገልግሎቱን ቢሮዎች ተዘዋውረው የተመለከቱ ሲሆን የአክሬዲቴሸን አገልግሎት ከፍተኛ የቢሮ ጥበት ችግር እንዳለበት መረዳታቸውንና በተለይ በዚህ በኮቪድ ወቅት በእንዲህ አይነት ሁኔታ ስራ መስራት አስቸጋሪ እንደሆነ መረዳታቸውን በመጥቀስ ችግሩ ሊፈታ ይገባል ብለዋል፡፡
ቋሚ ኮሚቴው ከተቋሙ ጋር ተቀራርቦ እንደሚሰራና በቀጣይ ግንኙነቶቹ እንደሚጠናከሩ የገለጹት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወ/ሮ አይሻ ያህያ ስለ አክሬዲቴሸን በቂ ግንዛቤ ለመያዝም በተቋሙ በኩል አስፈላጊው ድጋፍ ከተቋሙ እንደሚጠበቅ ጠቁመው ተቋሙ እያከናወናቸው ስላሉት ተግባራት በቂ መረጃ ማግኘታቸውን አመልክተዋል፡፡
በቢሮ ጥበት ረገድ በመንግስት እየተገነቡ ያሉት የጥራት መሰረተ ልማት ተቋማት ችግሮችን በቀጣይ ይፈታል የሚል እምነት እንዳለ የተናገሩት ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የብሔራዊ ጥራት መሰረተ ልማት ተ/ተ/ዳይሬክተር አቶ ሳሙኤል አለነ ህንፃዎቹ በተጠቀሰው ጊዜ ባለመጠናቀቃቸው የተቋሙ ቢሮ ችግር ምክንያት እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡
መንግስት ተቋራጩ ያሉበትን የተለያዩ ችግሮች በመፍታት ሕንጻዎቹ ተጠናቀው ለታለመላቸው ዓላማ እንዲውሉ ጥረት እያደረገ እንደሆነም ገልፀዋል፡፡