መስከረም 22 ቀን 2016ዓ.ም አዲስአበባ
የኢትዮጵያ አክሬዲቴሽን አገልግሎት በምርት ሰርቲፊኬሽን እና በካሊብሬሽን ላቦራቶሪ አክሬዲቴሽን ዓለም አቀፍ እውቅና አገኘ፡፡
የአፍሪካ አክሬዲቴሽን ትብብር መስከረም 14-18 ቀን 2016ዓ.ም በኬንያ ናይሮቢ ባደረገው 14ኛው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ባደረገው ስብሰባ ለኢትዮጵያ አክሬዲቴሽን አገልገሎት በሕክምና ላቦራቶሪ ፣በፍተሻ ላቦራቶሪ ፣ በኢንስፔክሽ አክሬዲቴሽን እንዲሁም በሥራ አመራር ሥርዓት የጥራት ሥራ አመራር ንዑስ ዘርፍ ቀድሞ ከሰጠው ዓለም አቀፍ ዕውቅና በተጨማሪ በካሊብሬሽን ላቦራቶሪ እና በምርት ሰርቲፊኬሽን ዕውቅና መስጠቱን አስታውቋል፡፡ ይህም አገልግሎቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ያገኘባቸው የአክሬዲቴሽን ዘርፎችን ወደ ስድስት አሳድጎታል፡፡
አገልግሎቱ በሁለቱ አዲስ የአክሬዲቴሽን ዘርፎች አዲስ ዕውቅና ለማግኘት እንዲሁም በሶስቱ ዘርፎች የነበረውን ዕውቅና ለማስቀጠል የቻለው በግንቦት 2015ዓ.ም ስምንት አባላትን የያዘ የአፍሪካ አክሬዲቴሽን ትብብር የግምገማ ብድኑ አባላት በኢትዮጵያ አክሬዲቴሽን አገልግሎት በመገኘት የአገልግሎቱን አሰራር ፣አደረጃጀት እና ሌሎችም ተያያዝ ጉዳዮችን ለ5 ቀናት በመገምገም እና በግምገማው በቡድኑ የተገኙ ክፍተቶችን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ አገልግሎቱ እንዲስተካክል በተሰጠው አቅጣጫ መሰረት ተግባራዊ በማድረጉ ነው፡፡
የተገኘው ዕውቅና የተስማሚነት ምዘና ተቋማት ብቃታቸውን በማረጋገጥ የአገራችንን የወጪ እና የውስጥ ንግድ ጥራትን በማስጠበቅ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን እንደሚያሳድግ የኢትዮጵያ አክሬዲቴሽን አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ቦንሳ ባይሳ ገልጸው ዕውቅናው እንደተቋም ብቻ ሳይሆን እንደ ሃገር ትልቅ ስኬት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የካሊብሬሽን ላቦራቶሪ ዕውቅናን ከውጭ ተቋማት ሲያገኙ የነበሩ የአገራችን የተስማሚነት ምዘና ተቋማት እና የኢትዮጵያ ስነ-ልክ ኢንስቲትዩት በአገር ውስጥ ከኢትዮጵያ አክሬዲቴሽን በተመጣጣኝ ክፍያ ማግኘት እንደሚያስችላቸው ዋና ዳይሬክተሩ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
የአፍሪካ አክሬዲቴሽን ትብብር የአክሬዲቴሽን አካላት፣ የክፍለ አህጉራዊ የአክሬዲቴሽን ትብብር እና የባለድርሻ አካላት በጋራ የተቋቋመ ሲሆን ከአለም አቀፉ የአቻ ተቋማት ጋር በጋራ የሚሰራ በአፍሪካ ንግድን ለማቀላጠፍ፣ ጤና፣ደህንነትና አካባቢን በመጠበቅ የአፍሪካን በዓለም ተወዳዳሪነት ለማሳደግ ዓላማ አድርጎ የሚሰራ ነው፡፡