ያለጥራት ውድድር ሊታሰብ የማይችል በመሆኑ ጥራትን ማስጠበቅ የሁሉም አካላት አንገብጋቢ ጉዳይ ሊሆን እንደሚገባ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ክቡር ዶር. ካሳሁን ጎፌ ገለጹ፡፡ ይህንን የገለጹት ሚኒስቴሩ ከነሀሴ 19-23፣2016 ዓ.ም ድረስ “የኢትዮጵያን ይግዙ” በሚል መሪ ቃል ያዘጋጀው የንግድ ሳምንት አካል በመሆን ነሀሴ 22 ቀን ስለ ጥራት የመከረውን የፓናል ውይይት በከፈቱበት ወቅት ነው፡፡
የሀገር ውስጥና የወጪ ንግዱን በማገርነት ያስተሳሰረው የጥራት ጉዳይ ነው ያሉት ሚኒስትሩ የምርትና የአገልግሎት ጥራትን መቆጣጠር እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አዳጊ ኢኮኖሚዎች ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡
ዶር. ካሳሁን፣ ማምረት ብቻውን ብቻውን በቂ እይደለም፤ በጥራት ማምረት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ያሉ ሲሆን፣ ከዚህ አኳያ ሀገሪቱም በማምረት ላይ የተረባረበችውን ያህል በጥራትም ላይ እየሰራች መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ለዚህም በጥራት መሰረተ ልማት ፕሮጀክት በ5.7 ቢልየን ብር አስፈላጊ መገልገያ መሳሪያዎች የተገጠሙላቸው 13 ህንጻዎች ግንባታቸው በቅርቡ ተጠናቆ የሚመረቁ መሆኑ አይነተኛ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ክቡር ሚኒስትሩ በአደረጃጀት ደረጃም ሀገራችን ከጥራት ጋር የተያያዙ የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት፣ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት፣ የስነ ልክ ኢንስቲትዩት እና የኢትዮጵያ አክሬዲቴሽን አገልግሎት ያሏት መሆኑን አስታውሰዋል፡፡
በፓናል ውይይቱ ወቅት የኢትዮጵያ አየር መንገድና የኢትዮጵያ የጥራት ሽልማት ድርጅት የስራ ሀላፊዎችና ፕሮፌሰር ዳንኤል ቅጣው ተጋባዥ እንግዳ በመሆን በጥራት ዙርያ ያላቸውን ልምድና እውቀት ለመድረኩ ተሳታፊዎች አካፍለዋል፡፡
በፓናል ውይይቱ ላይ ተጋባዦቹ በአገልግሎትም ሆነ በምርት መስክ ጥራትን መሰረት አድርጎ መስራት እንደሚገባና ስለ ጥራት ግንዛቤ ያለው ህብረተሰብ ለመፍጠር መስራት እንደሚያሻ፣ የጥራትን ጽንሰ ሀሳብ ከመዋእለ ህጻናት እስከ ከፍተኛ ትምህርት ውስጥ ማስረጽም የዚሁ ስራ አካል መሆን እንደሚኖርበት ጠቅሰዋል፡፡
እንደዚሁም ጥራትን ከማምጣት ባለፈ የተደረሰበትን የጥራት ደረጃ ማስጠበቅ በተቋማት አመራሮች ዘንድ ያላሳለሰ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባና የደንበኞች አገልግሎትን በየወቅቱ እየገመገሙ አሰራርን ማሻሻል እንደሚያስፈልግ፣ ለዚህም የአመራሩ ቁርጠኝነት ወሳኝ መሆኑ ተመላክቷል፡፡ ፈጠራ የታከለበት አስተሳሰብንና ቴክኖሎጂን በመጠቀም ጥራትንና ተወዳዳሪነትን ማስቀጠል ትኩረት ሊቸረው እንደሚገባም ተጠቁሟል፡፡